አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑት የልማት ጉዳዮች መካከል ኢንቨስትመንት በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡

 

የክልሉን የኢንቨስትመንት እንቅስቀሴ ለማሳለጥ የኢንቨስትመንት አዋጁ ከወጣበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በመንግስት በኩል በተለያዩ ጊዜያት የህግ ማሻሻያዎች በማድረግ ባለሃብቶችን ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡  በዚህም በክልሉ ፈቃድ መስጠት በተጀመረበት በ1985 ዓ.ም በፕሮጀክት ቁጥር 25፣ በካፒታል መጠን ብር 73 ሚሊዮን 477 ሺህ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ 1692 የነበረው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ፍሰቱ በዓይነትም ሆነ በመጠን ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መጥቶ በአሁኑ ወቅት እስከ መስከረም 30/2001 ዓ.ም ድረስ ባለው መረጃ መሠረት የፕሮጀክቶች ቁጥር 3763፣ የካፒታል መጠን ብር 46 ቢሊዮን፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ደግሞ 842110 ሊደርስ ችሏል፡፡

 

በክልሉ ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻልና ዕድገት የሚታይበት ቢሆንም በክልሉ እንዲመጣ ከሚጠበቀው ልማትና ከደንበኛው ፍላጎት አንፃር ሲመዘን በቀጣይ በርካታ ሥራዎች መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡

 

በመሆኑም በክልሉ የሚታሰበውን ልማት ለማምጣትና ተወዳዳሪ የሆነ የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር እንዲቻል በኢንቨስትመንት በኩል የሚታዩ የአሰራርና የአደረጃጀት ችግሮችን በመለየት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ለማድረግ የሚያስችል የመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ጥናት ማካሄድ በማስፈለጉ “የልማታዊ ባለሃብት መሳብና መደገፍ አዲስ የሥራ ሂደት” ተቀርጿል፡፡

 

አዲሱ የሥራ ሂደት ከደንበኛው የልማት ፍላጐት በመነሳት ከዚህ በፊት በሥራ ሂደቱ በተበታተኑ ክፍሎችና በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ደንበኞችን ለወጪና ለጊዜ ብክነት ሲዳርጉ የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥን በተማከለ ቦታና በቅርበት እንዲያገኝ የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት ቀይሶ በቅርቡ ወደ ሙከራ ትግበራ ተሸጋግሯል፡፡

 

በሥራ ሂደቱ የሚከናወኑ ተግባራት

የሥራ ሂደቱ የደንበኛውን ፍላጎት በግብዓትነት በመውሰድ የሚከተሉትን አብይ ተግባራት ይፈጽማል/ እንዲፈፀሙ ያመቻቻል፡፡

1.      በሥራ ሂደቱ አቅም የሚጠኑ የኢንቨስትመንት ጥናቶችን ማጥናት፣ ከሥራ ሂደቱ አቅም በላይ የሆኑትን በኮንትራት ማስጠናት

2.      የሀብት መሠረትን፣ የፕሮጀክት ሃሳቦችን፣ ማበረታቻዎችንና ምቹ ሁኔታዎችን፣ የኢንቨስትመንት መሬትን የመሠረተ ልማትና የብድር እንዲሁም ሌሎች ኢንቨስትመንት ነክ መረጃዎችን  በመስጠት በክልሉ ሊያለሙ የሚችሉ ልማታዊ ባለሃብቶችን መመልመል

3.     ለተመለመሉ ልማታዊ ባለሃብቶች የፈቃድና ምዝገባ አገልግሎት መስጠት

-          የንግድ ስም ማጣራት፣

-          የንግድ ማህበራትን ማዋዋልና መመዝገብ

-          የኢንቨስትመንት ፈቃድ መስጠት

4.          የከተማ መሬት አቅርቦት

 

5.          የክትትልና ድጋፍ አገልግሎት

§         መሠረተ ልማት

§         ብድር

§         ስልጠና

§         የቴክኖሎጂና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች አቅርቦት እና

§         ሌሎች የገጠር መሬት አቅርቦት፣ ማበታቻዎችና የሙያ ድጋፎችን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲያገኙ ማስቻል/ማመቻቸት

§         የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም በመከታተል አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ

 

የሥራ ሂደቱ አደረጃጀት

የሥራ ሂደቱ ከዚህ በፊት በክልል፣ በሶስት የዞን ላይዘን ጽ/ቤቶችና በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች መስጠት የሚያስችል አደረጃጀት ዘርግቶ የሙከራ ትግበራ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

በክልል ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎች

§         ክልላዊ ይዘት ያላቸውን ጥናት ማጥናት/ማስጠናት

§         ለኢንቨስትመንት አጋዥ የሆኑ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በክልሉ ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃብቶችን መመልመል

§         ከአንድ ዞን በላይ ለሚሸፍኑ ፕሮጀክቶች  የፈቃድና የምዝገባ አገልግሎት መስጠት

§         በክልል፣ በዞኖችና በከተማ አስተዳደሮች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለተሰጣቸው ኘሮጀክቶች  አስፈላጊውን

§         ድጋፍ መስጠትና ለውጤት ማብቃት

§         በዞኖችና በከተሞች የሚገኙ የሥራ ሂደቱ አስፈፃሚ አካላትን በስልጠናና በቁሳቁስ በማገዝ አቅማቸውን መገንባት

 

በአዲስ አበባ ላይዘን ጽ/ቤት የሚሰሩ ስራዎች

 

§         በኢንቨስትመንት አጋዥ የሆኑ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በክልሉ ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃብቶችን መመልመል

 

በዞን ደረጃ የሚሰሩ ሥራዎች

§         ዞናዊ ይዘት ያላቸውን ጥናቶች ማጥናት

§         ለኢንቨስትመንት አጋዠ የሆኑ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በዞኑ ሊያለሙ የሚችሉ ልማታዊ ባለሃብቶችን መመልመል

§         በዞኑ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የፈቃድና ምዝገባ አገልገሎት መስጠት

§         በዞኑ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለወሰዱ ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ወደ አፈፃፀም ማሸጋገር

 

በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚሰሩ

ሥራዎች

§         በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚጠኑ ጥናቶችን ማካሄድ

§         ለኢንቨስትመንት አጋዥ የሆኑ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በከተማው ለማልማት የሚችሉ  ልማታዊ ባለሃብቶችን መመልመል

§         በከተማው ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የፈቃድና ምዝገባ አገልግሎት መስጠት

§         ለከተማው የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለወሰዱ ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ወደ አፈፃፀም ማሸጋገር

 

በአጠቃላይ የሥራ ሂደቱ በክልል፣ በዞንና በከተማ አስተዳደሮች በሚኖረው አደረጃጀት አገልግሎቶችን ለደንበኛው ለመስጠት የሰው ኃይል፣ ቢሮና ቁሳቁስ የማሟላት ሥራዎችን በማካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎቱን በአብዛኞቹ ዞኖችና ከፊል በከተሞች በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡  ስለሆነም የሥራ ሂደቱ ደንበኞች የሚፈልጉትን አገልግሎትና ድጋፍ የሥራ ሂደቱ ባለው አደረጃጀት አማካኝነት ማግኘት የሚችሉ መሆኑን እየገለጽን ለተጀመረው የሙከራ ትግበራ በሥራ ሂደቱ ቀጥተኛ የመሠረተ ልማትና የብድር እንዲሁም የገጠር መሬት አቅርቦት እና ሌሎች የሙያ ድጋፍ ሰጪ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የተቀናጀ አሰራር፣ የተቀላጠፈ የአገልግሎቶችና ድጋፍ አሰጣጥ ለሥራ ሂደቱ ስኬታማነት ሚናቸው ወሳኝ በመሆኑ በጋራም ሆነ በተናጠል የተጣለብንን አደራ በመወጣት ክልላችንን የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ የነቃ ተሳትፎና ያልተቆጠበ እገዛችንን በለውጥ ቅኝት አጠናክረን እንቀጥል፡፡